Tuesday, September 05, 2006

በሃረሪ ከ16ሺህ የሚበልጡ አርሶአደሮች በሴፍትኔት መርሀ ግብር እየተሳተፉ ነው

ሐረር ነሐሴ 29 /1998/ዋኢማ/በሐረሪ ህዝብ ክልል የምግብ ዋስትና ችግር ጎልቶ በሚታይባቸው 17 የገጠር ቀበሌዎች በተጠናቀቀው አጋማሽ የተጀመረው የሴፍቲኔትና የምግብ ዋስትና መርሀ ግብር አበረታች ውጤት እያስገኘ መሆኑን የክልሉ ገጠርና ግብርና ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አብዱርቃድር አደም ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት ከክልሉ መንግስት በተመደበ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በሚበልጥ ወጪ ገንዘብና ከ8ሺ ኩንታል በሚበልጥ እህል የተጀመረው የሴፍትኔት መርሃ ግብር 16ሺ 136 አርሶአደሮች ታቅፈው በተለያዩ አዋጭነት ባላቸው የምግብ ዋስትና ሥራዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

አርሶአደሮቹ እየተሳተፉባቸው ከሚገኙባቸው መርሀ ግብሮች መካከልም የጓሮ አትክልት ልማት፣ የሰብል ልማት፣የእንስሳት እርባታ፣ የድህረ ምርት ቴክኖሎጂ እንዲሁም የአፈርና ውሀ ጥበቃ ሥራዎች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

እንዲሁም በአነስተኛ ግድብ ሥራ፣ በኩሬና ውሀ ማቆር፣በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ፣ በመንገድ፣ በእርከንና በተለያዩ ተፋሰስ ሥራዎች ላይ ተሳትፎ በማድረግ ላይ መሆናቸውን የቢሮው ኃላፊ አቶ አብዱርቃድር አስረድተዋል።

አርሶአደሮቹ በመርሀ ግበሩ ታቅፈው እያደረጉ ባሉት የልማት እንቅስቃሴ በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ሰብሎችን በማምረት የነበረባቸውን የምግብ ዋስት ችግር በማቃለል ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

እንዲሁም ህብረተሰቡ ገንዘቡንና ጉልበቱ በማስተባበር ተሳትፎ በማድረግ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመርሀ ግብሩ በእንስሳት እርባታና ልማት ሥራዎች ለሚሳተፉ አርሶአደሮችና አርብቶአደሮች የክበድ ላሞች፣እርጉዝ ፍየሎች ተገዝተው እየተሰራጩ መሆናቸውንም አቶ አብዱል ቃድር አመልክተዋል።

0 Comments:

Post a Comment

<< Home