Thursday, September 14, 2006

የክልሉ የጤና አገለግሎት ሽፋን 89ነጥብ6 በመቶ መድረሱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ

ሐረር መስከረም 4 /1998/ዋኢማ/የሐረሪ ህዝብ ክልል የጤና አገልግሎት ሽፋን 89ነጥብ6 በመቶ መድረሱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሀላፊ ዶክተር ካሣ ሀይሉ ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው ዓመት 76 ነጥብ 4 በመቶ የነበረው የክልሉ የጤና አገልገሎት ሽፋን ዘንድሮ 89 ነጥብ6 በመቶ ደርሷል።

የክልሉ የጤና አገልግሎት ሽፋን ከአምናው በ12 በመቶ መጨመሩን ጠቁመው፤ሊጨምር የቻለውም በክልሉ የገጠርና ከተማ ቀበሌዎች ሲካሔዱ ከነበሩት 12 ፕሮጀክቶች መካከል ዘጠኙ ግንባታቸው ተጠናቆ በዚህ ዓመት ለአገልግሎት በመብቃታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ከመንግስት በተመደበ 6ሚሊዮን 27ሺ352 ብር ተገንብተው ለአገልግሎት ከበቁት የጤና ተቋማት መካከልም ስድስት ጤና ኬላዎችና ሁለት የምክር አገልገሎት መስጫ ማዕከላት እንደሚገኙበት ዶክተር ካሳ ገልጸዋል።

እንዲሁም የሁለት ሆስፒታሎችን የክፍል ጥበት ለማቃለልና የአገለግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት፣ የተለያዩ የህክምና አገለግሎት መስጫ መሳሪያዎች፣የመማሪያ መጻህፍትና የትምሀርት መርጃ ቁሳቁስ ግዥ፣እንዲሁም የውስጥ ቁሳቁስ ማሟላት ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።

ከዚህም ሌላ የምስራቅ አርበኞች ሆስፒታል የጀነሬተር ግዥ፣የህይወት ፋና ሆስፒታል ካርድና ፋርማሲ መጋዘን ክፍል ግንባታ፣የነርስ ማሰልጠኛ ተቋም ማሻሻያ፣ የመማሪያ ክፍል ግንባታ ሥራዎች በመካሔድ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በዚህ ዓመት ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁ ተናግረዋል።

በተጨማሪ በክልሉ ከሁለት ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ በልዩ ልዩ ምክንያቶች የግንባታ ሥራው ተጓቶ የነበረው የ4ኛ ጤና ጣቢያ ግንባታ ሙሉ በመሉ መጠናቀቁንም ዶክተር ካሳ ጠቁመው የጤና ተቋማቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ ከ30 ሺ ለሚበልጡ ሰዎች አገልግሎት እንደሚሰጡ አስረድተዋል።

ቢሮው ባለፈው ዓመትም ከመንግስት በተመደበ አምስት ሚሊዮን ብር ወጪ የ13 ፕሮጀክቶችን ግንባታ አጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃቱንም ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
(c) Walta Information Center, Addis Ababa, Ethiopia

0 Comments:

Post a Comment

<< Home