Monday, September 25, 2006

በሐረሪ ህዝብ ክልል 85 ፕሮጀክቶች እንደሚገነቡ ተገለጸ

ሐረር መስከረም 14/ 1999 /ዋኢማ/ በሐረሪ ህዝብ ክልል ዘንድሮ ከ50 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር በሚበልጥ ወጪ የ85 አዲስና ነባር ፕሮጀክቶች ግንባታ እንደሚካሔድ የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አሪፍ አብዱል ሀፊዝ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤የፕሮጀክቶቹ ግንባታ የሚካሔደው በክልሉ 19 ከተሞችና 17 የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ነው።

ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ከሚካሔዱት ፕሮጀክቶች መካከል ከግማሽ የሚበልጡት አዳዲስ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን አቶ አሪፍ ጠቁመው፤የትምህርት፣ ጤና፣ውሀ፣ ግብርና፣ ከተማ ልማት፣ አቅም ግንባታና መንገድ ሥራዎች እንደሚገኙበት አስታውቀዋል።

በክልሉ 12 አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችና በዘጠኝ የቀበሌ አስተዳደሮች አማካኝነት የሚከናወኑት ፕሮጀክቶች በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ሲጠናቀቁ 100 ሺ የሚጠጉ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል።

ለፕሮጀክቶቹ ማስፈፀሚያ የሚውለው 46 ሚሊየን 749 ሺ 700 ብር ከመንግስት ፣ 1ሚሊዮን 810 ሺ ብር በእርዳታ፣1 ሚሊዮን 600 ሺ ብር ደግሞ በብድር የሚሸፈን መሆኑን አቶ አሪፍ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ቢሮው ለአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች በወቅቱ በጀት በመስጠት፣ ተገቢውን ክትትልና ግምገማ በማድረግ ድጋፍ እንደሚያደርግ የቢሮው ሀላፊ አስረድተዋል።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ44 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ከተጀመሩት 67 ነባርና አዲስ ፕሮጀክቶች መካከል አብዛኞቹ መጠናቀቃቸውንም ከአቶ አሪፍ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል።
(c) Walta Information Center, Addis Ababa, Ethiopia

0 Comments:

Post a Comment

<< Home