Wednesday, August 27, 2008

ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ብድር የተገዛ የቧንቧ እቃ በጅቡቲ ወደብ ተወረሰ

Tuesday, 26 August 2008


በተሾመ ንቁ

ለሐረር የመጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ብድር የተገዛ የቧንቧ ቁሳቁስ በጅቡቲ ወደብ መወረሱ ታወቀ፡፡ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቁም ታውቋል፡፡

በውሃ ሃብት ሚኒስቴር ተቆጣጣሪነት የተገዛው ለሐረሪ ከተማ የመጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት የሚውለው ቧንቧና የቧንቧ መለዋወጫ ቁሳቁስ በጅቡቲ ወደብ መወረሱን የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በምንጮቻችን ገለፃ መሰረት ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ የብድር ገንዘብ የተገዛው ቧንቧ በወደቡ ባለቤቶች ተወርሷል፡፡

የቧንቧ ቁሳቁሱን ለመግዛትና ሐረር ከተማ ድረስ ለማቅረብ ጨረታውን ያሸነፈው ዋት ኢንተርናሽናል የተባለ አገር በቀል ድርጅት እቃውን በውሉ መሰረት አላቀረበም፡፡ እንደ ምንጮቻችን ገለፃ ድርጅቱ ጨረታውን በማሸነፉ ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ የቅድመ ክፍያ ገንዘብ ወስዷል፡፡ በውሉ መሰረት ድርጅቱ እቃውን በመግዛት በጅቡቲ ወደብ መጋዘን ውስጥ ለረዥም ጊዜ ማስቀመጡና የወደብ ኪራዩ ከእቃው ዋጋ በላይ በመሆኑ መወረሱ ተገልጿል፡፡

የወደቡ አስተዳዳሪ ዱባይ ኢንተርናሽናል እቃው ባለመነሳቱ እቃውን በመውረስ መሸጡ ታውቋል፡፡ የወደቡ አስተዳዳሪ የተወረሰውን ቧንቧ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ነጋዴዎች በጨረታ መሸጡንም በጨረታው ከተካፈሉ ነጋዴዎች ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ለተወረሰው የቧንቧ ዕቃ መግዣ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን የጠቀሱት ምንጮቻችን፤ የፌዴራል መስሪያ ቤቱ ፕሮጀክቱን ከመከታተል አኳያ ድክመት እንደታየበት ጠቁመዋል፡፡ ከአፍሪካ ልማት ባንክ የብድር ፈቃድ ለማግኘት ከአንድ ዓመት በላይ እንደሚፈጅ በመጥቀስ ከፍተኛ የጊዜ ክስረት መድረሱን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም መሰል ብድር ለማግኘትና የግዢ ጨረታ ለማውጣት በሚደረግ ጥረት ፕሮጀክቱ እንደሚጓተት አስታውቀዋል፡፡

የግዢ ጨረታው አለም አቀፍ ደረጃ በመሆኑ ለጨረታው የወጣው ወጪ መክሰሩን፣ ፕሮጀክቱ ተፈፃሚ ቢሆን ከሐረር ከተማ በተጨማሪ የሀሮማያ፣ የአወዳይ፣ የአዴላና የደንገጎ ከተሞች ተጠቃሚ ይሆኑ እንደነበር ነገር ግን ሳይሳካ መዘግየቱን ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ሐምሌ 1997 ሲጀመር በ20 ወራት ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደነበረ ያወሱት ምንጮቻችን እስከ አሁን ባለመጠናቀቁ ማዘናቸውን ገልፀዋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የሐረር የመጠጥ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የእቅድና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቡሽራ መሀመድረሺድ ባለስልጣኑ ጉዳዩን እንደማያውቅ ገልፀዋል፡፡ ባለስልጣኑ የቧንቧ ግዢውም ሆነ የፕሮጀክቱን ሁኔታን እንደማይመለከተው አስታውቀዋል፡፡ አቶ ቡሽራ ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ የሚገዛው ቧንቧ በቅርቡ ወደ ሐረር ከተማ ይገባል በሚል እየተጠባበቁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በፌዴራል የውሃ ሀብት ሚኒስቴር የሐረር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ታምራት ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቁን አምነዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ከ71 ኪሎ ሜትር በላይ የሚፈጅ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፣ የካሳ ክፍያ ሂደት ጊዜ መፍጀቱን ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ግዢ ሂደት ላይ የተፈጠረ መዘግየት፣ በዲዛይን ሥራ ላይ በተከሰተ ችግር፣ በሲሚንቶ እጥረት ምክንያት የኮንስትራክሽን ሥራ መደናቀፉን ጠቅሰዋል፡፡

አቶ ጌታቸው በተጠቀሱት ምክንያቶች ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቁንና በሚቀጥለው መስከረም ወር ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል፡፡ በጅቡቲ ወደብ ስለተወረሰው የፕሮጀክቱ እቃን በተመለከተ የማይመለከታቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

0 Comments:

Post a Comment

<< Home