Monday, January 14, 2008

News release from Haddeed Secretary

ለሐረሪ ሕዝብ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲ ተቋቋመ Print E-mail
Sunday, 13 January 2008
ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው የሐረሪ ክልል ተወላጆች የፖለቲካ ፓርቲ በማቋቋም ለክልሉ ተወላጆች አማራጭ የፖለቲካ ፕሮግራም ይዘው መቅረባቸውን አስታወቁ፡፡ የአዲሱ ፓርቲ ፀሐፊ ክልሉን በማስተዳደር ላይ ያለው ፓርቲ መስራችና ስራ አስፈፃሚ ነበሩ፡፡

የሐረሪ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ሐዲድ) በመባል የተቋቋመው ፓርቲ ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ታህሳስ 24 ቀን 2000 ዓ.ም የምስክር ወረቀት አግኝቷል፡፡

ፓርቲው የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ማግኘቱን ተከትሎ ዋና ፀሐፊው አቶ ኤሊያስ ጠሀ ሸሪፍ ለሪፖርተር እንደገለፁት "ለሐረሪ ሕዝብ አማራጭ የፖለቲካ ፕሮግራም ይዘን ቀርበናል" ብለዋል፡፡

በሐረሪ ክልል ከገዢው ፓርቲ ሌላ አማራጭ ባለመኖሩ ሕዝቡ የሚፈልገውን የመምረጥ እድል ሳያገኝ ለዓመታት መኖሩን የገለፁት ዋና ፀሐፊው "በሚቀጥለው ምርጫ ህዝቡን ከአንድ ፓርቲ ጥገኝነት እናላቅቀዋለን፡፡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የፈለገውን እንዲመርጥ ከአሁኑ ጀምሮ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን" በማለት ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ላለው የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ፕሮግራም እንደተዘጋጀ የገለፁት የሐዲድ ዋና ፀሐፊ በሚያዚያ ወር በሚካሄደው የማሟያ ምርጫ ሕዝቡ በንቃት ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ ነገር ግን በምርጫው እንደማይሳተፉ ገልፀዋል፡፡

የሐረሪን ክልል እያስተዳደረ ያለው የሐረሪ ብሄራዊ ሊግ (ሐብሊ) ሲሆን አዲስ በተቋቋመው ፓርቲ ውስጥ የቀድሞ የሐብሊ አባላትና መስሪያዎች እንደሚገኙበት የገለፁት ዋና ፀሐፊው "ለሐረሪ ሕዝብ አማራጭ ፖለቲካ ፕሮግራም መያዛችንን አሳምነን ደጋፊዎቻችንን በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲመርጡ አስተምረን ከሁለት ዓመት በኋ በሚደረገው አገራዊ ምርጫ እንወዳደራለን" ብለዋል፡፡ አያይዘውም መሰረት ያለው የምርጫ ስራ ሳይሰራ ወደ ምርጫ መግባቱ ፓርቲያቸው እንደማያምንበትም ተናግረዋል፡፡

በአሰግድ ተፈራ